TM Law Firm Accessibility
×

መዝገቡ የቀረበው፡ ለፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን
ጉዳዩ፡ "GAULAC" የሕጻናት ወተት የቀረጥ ዋጋ በሕግ አግባብ አልተተመነልኝም የሚል ነው
ይግባኝ ባይ፡ ቲ ኤም የጥብቅና እና የህግ ምክር አገልግሎት ድርጅት ስለ ሬንጀር ኢንዱስትሪ እና ትሬዲንግ ኃላ/የተ/የግ/ማህበር
መልስ ሰጪ፡ ጉምሩክ ኮሚሽን የሞጆ ቅርንጨፍ /ቤት
የይግባኝ ባይ የቅሬታ ነጥቦች 

ይግባኝ ባይ ሬንጀር ኢንዱስትሪ ኃላ/የት/የግ/ማህበር ፈረንሳይ የሚመረተውን "GAULAC" የተባለ የጨቅላ ሕፃናት ወተት (ዱቄት) ወደ አገር ውስጥ ላስገባቸው ዕቃዎች የግብይት ዋጋ አቅርቦ የነበረ ሲሆን መልስ ሰጭ በበኩሉ ይህንን ያቀረበውን ዋጋ መርምሮ ከጉምሩክ የዋጋ መረጃ ቋት (ዳታ ቤዝ) ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑን በመግለጽ ውድቅ በማድረግ ሚዛናዊ የተመሳሳይ ዋጋ አተማመን ዘዴን በመጠቀም ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ዕቃዎች ላይ ተቀባይነት ካገኙ ዋጋዎች ጋር በማነጻጸር 3.15 ዶላር የነበረውን 10.13 ዶላር በማድረግ በአንድ እቃ ዋጋ ወስኗል፡፡ ይግባኝ ባይ ይህንን የመልስ ሰጪን ውሳኔ በመቃወም ጉዳዩን ለግብር ይግባኝ ኮሚሽን አቤቱታ ድርጅታችን እንዲያቀርብላቸው ጠይቀው ጉዳዩ ክርክር ከተደረገበት በኋላ  የሚከተለውን ውሳኔ አግኝቷል።

የይግባኙ አላማ

ይግባኝ ባይ ያስመጣው "GAULAC" የጨቅላ ሕጻናት ወተት የዕቃው ሞዴል እና አይነት በአግባቡ ተረጋግጦ ያቀረብነው ማስረጃ ታይቶ የገባውን ወተት አይነቱን እና ብራንዱን ባገናዘበ መልኩ የጉምሩክ የቀረጥ ክያ ዋጋ በገዙበት  ተስተካክሎ እንዲሰጣቸው ማድረግ ነው።

በክርክሩ የተነሱ ዋና ዋና የይግባኝ ባይ ነጥቦች

ü  መልስ ሰጭ ያቀረብነውን የግብይት ዋጋ ውድቅ ያደረገው በመመሪያ ቁጥር 158/2011 አንቀጽ 25(2)(-) በተደነገጉት ምክንያቶች መሰረት ሳይሆን ከዳታ ቤዝ ጋር በማነጻጸር ብቻ ነው ይህም ህጉን የጣሰ ነው፡፡

ü  መልስ ሰጪ ለማነጻጸሪያነት የተጠቀሙባቸው ዕቃዎች (INFANT FORMULA እና FOLLOW-ON-FORMULA) አኛ ያስገባነው "GAULAC" ዕቃ ጋር ተመሳሳይ አይደሉም፡፡ እኛ ያስገባነው GAULAC በፈረንሳይ የሚመረት ሲሆን በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተፈላጊነት ከሌሎቹ ዝቅተኛ በመሆኑ ዋጋውም ዝቅተኛ ነው፡፡

ü  ዕቃውን ከአምራቹ በቀጥታ የገዛን መሆናችንን የሚገልጽ የአምራች ድርጅት ዝርዝር እና የዋጋ ዝርዝር ማቅረብ ብንፈልግም መልስ ሰጭ እንድናቀርብ እድል አልሰጠንም፡፡

ü  የአምራቹ ብቸኛ አስመጪ መሆናችንን የሚገልጸውን ውል አቅርበን  በዝምታ ታልፏል እዲሁም ቀደም ሲል በተለየ አጋጣሚ የተሰጠ ውሳኔን በተመለከተ ከዚህ በፊት በዲክላሬሽን ቁጥር 19887/2024 ተመሳሳይ ዕቃ አስገብተን ባቀረብነው ዋጋ (2.83 ዶላር) ተቀባይነት አግኝተን ነበር፡፡

ü  የጉምሩክ አቤቱታ አጣሪ ዳይሬክቶሬት ሚያዝያ 1/2017 . በሰጠው ውሳኔ የሕፃናት ወተቶች በገበያ ተፈላጊነታቸው እንደሚለያዩ በመግለጽ በአምራች ዋጋ ዝርዝር መሰረት እንድንስተናገድ ወስኖልን ነበር፡፡ አሁን ግን ያለ ምንም ምክንያት የተለየ ውሳኔ መስጠቱ ፍትሐዊ አይደለም፡፡

ü  የጉምሩክ አቤቱታ አጣሪ ዳይሬክቶሬት ሚያዝያ 1/2017 . በሰጠው ውሳኔ የሕፃናት ወተቶች በገበያ ተፈላጊነታቸው እንደሚለያዩ በመግለጽ በአምራች ዋጋ ዝርዝር መሰረት እንድንስተናገድ ወስኖልን የነበረ ሲሆን  አሁን ግን ያለ ምንም ምክንያት የተለየ ውሳኔ መስጠቱ ፍትሐዊ አይደለም፡፡

ü  የዋጋ አማካይ አለመውሰድን በተመለከተ በመመሪያ ቁጥር 158/2011 አንቀጽ 8(5) እና 9(5) መሰረት በርካታ የዋጋ መረጃዎች ሲኖሩ አማካይ ዋጋ መውሰድ ይገባል፡፡ ነገር ግን መልስ ሰጭ የተለያዩ ዋጋዎችን አማካይ ሳያደርግ ውሳኔ ማስተላለፉ ህጉን የጣሰ አሰራር ነው፡፡

በመልስ ሰጪ የቀረበ መልስ ዋና ዋና ነጥቦች

ü  የግብይት ዋጋ ውድቅ መደረግን በተመለከተ ይግባኝ ባይ ያቀረበው የግብይት ዋጋ ከጉምሩክ የዋጋ መረጃ ዳታ ቤዝ ጋር ሲነጻጸር አንሶ በመገኘቱ በመመሪያ ቁጥር 158/2012 አንቀጽ 12(1)() መሠረት ሚዛናዊ የተመሳሳይ ዋጋ አተማመን ዘዴን በመጠቀም ውሳኔ መስጠቱ ህጋዊ ነው፡፡

ü  የተነጻጸሩት ዕቃዎች በአዋጁ በተመለከተው የተመሳሳይ ዕቃ ትርጓሜ መሰረት ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ሁለቱም ዕቃዎች "INFANT FORMULA  400GX12 TINS" እና "FOLLOW-ON-FORMULA 400GX12 TINS" በማለት ተመሳሳይ ስያሜ ያላቸው እንዲሁም ሁለቱም ከፈረንሳይ የተመረቱ ናቸው፡፡

ü  ይግባኝ ባይ በኦንላይን ሲስተም አስተያየት እንዲሰጡ እና የቀረበው ዋጋ ትክክለኛ መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃ እንዲያቀርቡ እድል ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ይግባኝ ባይ በዋጋው አለመስማማታቸውን ብቻ በመግለጽ ዕቃዎቹን በዲፖዚት ማስለቀቅ እንደሚፈልጉ አመልክተዋል እንጂ ማስረጃ አላቀረቡም፡፡

ü  ቀደም ሲል የተሰጠ ውሳኔን በተመለከተ ውሳኔው የተሰጠው አስመጪው ባቀረበው ማስረጃ መሰረት ነው፡፡ የጉምሩክ ዋጋ የሚተመነው በዳታ ቤዝ መረጃ መሰረት እንጂ በሌሎች ውሳኔዎች አይደለም ውሳኔው በዳታ ቤዙ ላይ ለሪፈረንስነት እስካልገባ ድረስ ለሌሎች ዕቃዎች ተፈጻሚ አይሆንም፡፡

ü  የዋጋ አማካይ አለመውሰድን በተመለከተ አማካይ ዋጋ የሚወሰደው ከሁለት ወይም ከዚያ በላይ የተለያዩ ዋጋዎች ሲኖሩ ነው፡፡ እዚህ ጉዳይ ላይ ግን ሁለቱም ማነጻጸሪያዎች አንድ አይነት ዋጋ (10.13 ዶላር) ያላቸው በመሆኑ አማካይ ማስላት አላስፈለገም፡፡

  የይግባኝ ኮሚሽኑ ውሳኔ

ኮሚሽኑ እንደተረዳው የተነጻጸረው ዕቃ ከጨቅላ ሕፃናት ወተት ጋር በመሆኑ ብቻ ከተመሳሳይ እቃ ጋር ተነጻጽሯል ለማለት አይቻልም በማለት የገለጸ ሲሆን በይግባኝ ባይ የቀደመው ዋጋ ተሽሮ ወደ ሀገር ውስጥ የገባው ወተት አይነቱን እና ብራንዱን ባገናዘበ መልኩ ዋጋ ተስተካክሎ እንዲሰጣቸው በኮሚሽኑ ተወስኗል።

ለውሳኔው መሰረት የሆኑ ዋና ዋና የክርክር ነጥቦች

ü  ይግባኝ ባይ ወደ ሀገር ያስገባው እቃ "GAULAC" የተባለ የተለየ ብራንድ ያለው የሕፃናት ወተት ነው፡፡

ü  መልስ ሰጪ ለማነጻጸሪያነት ያዋለው እቃ ብራንዱ ያልተገለጸ፣ "INFANT FORMULA 400GX12 TINS" እና "FOLLOW-ON-FORMULA 400GX12 TINS" ተብሎ የተገለጸ እቃ ነው፡፡

ü  ኮሚሽኑ ይግባኝ ባይ ያቀረበውን የግብይት ዋጋ ውድቅ በማድረግ በጉምሩክ የዋጋ መረጃ ቋት መሰረት ቀረጥ እና ታክስ የመወሰኑ አግባብ ሕጋዊ ነው ብሎ መደምደም አልቻለም ምክንያት ለማነጻጸሪያነት የተጠቀመባቸው ዕቃዎች ከይግባኝ ባይ ዕቃ ጋር ተመሳሳይ መሆናቸው አለመረጋገጡ ነው፡፡

በመጨረሻም ኮሚሽኑ ዕቃዎቹ ተመሳሳይ ናቸው ተብሎ ሊወሰድ እንደማይቻል እና  ከተመሳሳይ እቃ ጋር ያልተነጻጸረ በመሆኑ የመልስ ሰጭን ውሳኔ በመሻር ደንበኛችን ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባው ወተት አይነቱን እና ብራንዱን ባገናዘበ መልኩ ዋጋ ተስተካክሎ እንዲሰጣቸው ወስኗል።